መቅረዝ የጤና አገልግሎት አክሲዮን ማኅበር የአክሲዮን ሽያጩን ለማፋጠን የአክሲዮን ሻጭ ኤጀንት ሊጠቀም መሆኑ ተገለጸ

የቦርዱ ም/ሰብሳቢ እና የማርኬቲንግ ቡድን መሪ የሆኑት አቶ ተስፋየ ቢሆነኝ ዛሬ ጥቅምት 9 2013 .ም እንደተናገሩት ያቀድናቸውን እቅዶች በቶሎ ወደ ሥራ ለማስገባት የአክዮን ሻጭ ኤጀንት መጠቀሙ አስፈላጊ መሆኑን ተናገሩ፡፡ የአክሲዮን ማኅበሩ የማርኬቲንግ ቡድን ከሚሠራው ሥራ በተጨማሪ የአክሲዮን ሻጭ ኤጀንት መጠቀሙ የበለጠ ውጤታማ ሊያደርገን ስለሚችል ከአክሲዮን ሻጭ ኤጀንት ጋር መዋዋሉ አስፈላጊ መሆኑን ቦርዱ ስላመነበት ከዚህ በፊት ልምድ ያላቸውን በማወዳደር አንድ የአክሲዮን ሻጭ ኤጀንት መመረጡን እና ከተመረጠውም ድርጅት ጋር ውል ለመግባት ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡

መቅረዝ የጤና አገልግሎት አክሲዮን ማኅበር በቅርቡ ለቴርሺያሪ ሆስፒታል ግንባታ የሚሆነውን ቦታ ከመንግስት በሊዝ ሊጠይቅ መሆኑ ተሰማ

መቅረዝ የጤና አገልግሎት አክሲዮን ማኅበር በቅርቡ ለቴርሺያሪ ሆስፒታል ግንባታ የሚሆነውን ቦታ ከመንግስት በሊዝ ሊጠይቅ መሆኑ በጥቅምት 8 2013 .. ቦርዱ ባደረገው ስብሰባ ላይ መወሰኑን የቦርዱ ሰብሳቢ የሆኑት ዶ/ር ማኅተመ በቀለ ተናገሩ፡፡ በጥቅምት 1 2013 .ም በተወሰነው ውሳኔ መሠረት ጎን ለጎን የቴሺያሪ ሆስፒታል ግንባታው እንቅስቃሴ መጀመሩ ቅድሚያ የሚሰጠው ሥራ በመሆኑ ለዚሁ የሚሆን የኢንጂነሪነግ ቡድን በማቋቋም ወደ ሥራ መግባቱን ገልጸዋል፡፡ ለዚህ የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎችን የተቋቋመው ቡድን በአጭር ጊዜ አጥንቶ ለቦርዱ በማቅረብ ያስወስናል ብለው ተናግረዋል፡፡

መቅረዝ የጤና አገልግሎት አክሲዮን ማኅበር ካፒታል ለማሳደግ ውሳኔ አሳለፈ

መቅረዝ የጤና አገልግሎት አክሲዮን ማኅበር በጥቅም 1 2013 .ም ባካሄደው ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤ የድርጅቱን ካፒታል በብር 518 ሚሊዮን ለማሳደግ ወሰነ፡፡ አክሲዮን ማኅበሩ ይህንን ሊወስን የቻለበትን ጉዳይ የቦርዱ ሰብሳቢ የሆኑት ዶ/ር ማኅተመ በቀለ ሲያብራሩ መቅረዝ በአይነት እና በጥራት ለየት ያሉ የጤና አገልግሎቶችን ወደ ሀገራችን በማምጣት የሕሙማንን እንግልት መቀነስ እንዲሁም በዘርፉ የጤና ቱሪዝምን በማስፋፋት ለሀገር ገቢን ማስገኘትን አስቦ የሚንቀሳቀስ ነው፡፡ አክሲዮን ማኅበሩ በመጀመሪያው ዙር ሊሠራቸው ላሰባቸው ትላልቅ ሥራዎች ማለትም የጠቅላላ ሆስፒታል ፣ የዲያግኖስቲክ ማእከል፣ የመድኃኒት እና ሕክምና እቃዎች አስመጪ እና አከፋፋይ፣ ፋርማሲዎች እንዲሁም በጤና ጥናቶች እና ምርምሮች ላይ የሚሠራ ተቋም ለማቋቋም በመታሰቡ እነዚህን ለመሥራት የሚያስፈልገውን ካፒታል ለማግኘት ከባንክ ከሚገኘው ብድር በተጨማሪ ካፒታል ማሳደጉ አስፈላጊ እና ቁልፍ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አክሲዮኑንም የሚያሳድገው ለመሥራች ባለአክሲዮኖች እና ለሕዝብ በሚያወጣቸው ተራ አክሲዮኖች ሽያች መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተያያዘ ዜናም እስከ ታኅሳስ 30 2013 አክሲዮን የሚገዙ ባለአክሲዮኖችን እንደ መሥራች ባለአክሲዮኖች እንዲቆጠሩ ፤ ለመሥራቾች ባለአክሲዮኖች የሚሠጠው ጥቅምም 10 በመቶ እንዲሆን መወሰኑን እንዲሁም ተቋማቱ ሥራ ሲጀምሩ ሁሉም ባለአክሲዮኖች በቅናሽ አገልግሎት እንደሚያገኙ ተናግረዋል፡፡ በመጨረሻም ሲያብራሩ ‘’እኛ የምንፈልገው ሁሉም አክሲዮን የሚገዛ በሙሉ መሥራች ባለአክሲዮን እንዲሆን ነው ’’ ያሉት የቦርዱ ሰብሳቢው ሁላችሁም እስከ ታኅሳስ 30 ድረስ ከብር 20 ሺህ ጀምራችሁ በመግዛት መሥራች ባለአክሲዮን እንድትሆኑ በማለት ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

መቅረዝ የጤና አገልግሎት አክሲዮን ማኅበር አንደኛ መደበኛ እና አንደኛ ድንገተኛ ጉባኤው በደማቅ ሁኔታ አካሄደ

መቅረዝ የጤና አገልግሎት አክሲዮን ማኅበር እሁድ ጥቅምት 1 2013 ዓ.ም. አንደኛ መደበኛ እና አንደኛ ድንገተኛ ጉባኤውን በኢንተር ኮንቲኔንታል አዲስ ሆቴል አካሄዷል፡፡ በጉባኤውም ላይ ሼር ከገዙ ባለአክሲዮኖች 72 በመቶው በራሳቸው እና በተወካያቸው ተገኝተዋል፡፡ በቅርቡ በጤና ጥበቃ ባወጣው መመሪያ መሠረት በአንድ ቦታ ለስብሰባ መገኘት የሚችለው ሰው ከ 50 በታች መሆን ስላለበት በጉባኤውም ላይ በአጠቃላይ 45 የሚሆኑ ባለአክሲዮኖች ተገኛተዋል፡፡ በጉባኤውም ላይ የሚከተሉት አጀንዳዎች ከጸደቁ በኋላ በምልዓተ ጉባኤው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ አጀንዳዎቹም

የአንደኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ አጀንዳዎች

 1. የ1ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ አጀንዳዎች ማጽደቅ
 2. የአ/ማኅበሩን የምሥረታ ሪፖርት መስማት እና ማጽደቅ
 3. የ2013 በጀት ዓመትን የትኩረት አቅጣጫዎችን መገምገም እና ማጽደቅ
 4. የውጪ ኦዲተር መሠየም እና ክፍያውን መወሰን
 5. የመሥራች አባላትን ጥቅም መወሰን
 6. የቦርድ አባላትን ክፍያና ጥቅም መወሰን
 7. የዳይሬክተሮች ቦርድ ባለአክሲዮኖችን በመወከል በሰነዶች ማረጋገጫ መ/ቤት ተገኝተው ቃለ ጉባኤውን እንዲፈርሙ ውክልና ስለመስጠት
 8. የ1ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ቃለ ጉባኤውን ማጽደቅ

የአንደኛ ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤ አጀንዳዎች

 1. የ1ኛ ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤ አጀንዳዎች ማጽደቅ
 2. የአክሲዮን ማኅበሩን ካፒታል ማሳደግ
 3. የዳይሬክተሮች ቦርድ አዳዲስ የሚገቡ፣ የሚያዛውሩ እና አክሲዮን የሚያሳድጉ ባለአክሲዮኖችን በመወከል በሰነዶች ማረጋገጫ መ/ቤት ተገኝተው እንዲፈርሙ ውክልና ስለመስጠት
 4. አዲስ ባለአክሲዮኖችን እንደ መሥራች አባልነት እንዲመዘገቡ ማኅበሩ የሚቀበልበትን የጊዜ ገደብ መወሰን
 5. የ1ኛ ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤ ቃለጉባኤ ማጽደቅ

ከላይ በተቀመጡት አጀንዳዎች ላይ ሰፊና ጥልቅ ውይይት ከተካሄደ በኋላ ቦርዱ ያቀረባቸውን የውሳኔ ሃሳቦች በሙሉ ድምጽ ያለምንም ተቃውሞ በማጽደቅ ጠቅላላ ጉባኤው ከ ቀኑ 11፡30 ተጠናቋል፡፡