የመቅረዝ የጤና አገልግሎት አክሲዮን ማኅበር የመሥራችነት ጥቅም የሚያስገኘውን የአክሲዮን ሽያጭ እስከ መጋቢት 30 2013 ዓ.ም አራዘመ
የመቅረዝ የጤና አገልግሎት አክሲዮን ማኅበር የዳይሬክተሮች ቦርድ በ የካቲት 1 2013 ዓ.ም ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ የመሥራችነት ጥቅም የሚያስገኘውን የአክሲዮን ሽያጭ እስከ መጋቢት 30 2013 ዓ.ም ድረስ ማራዘሙን ገለጸ፡፡
የቦርዱ ሰብሳቢ የሆኑት ዶ/ር ማኅተመ በቀለ ሲናገሩ በተደጋጋሚ ከቀደምት መሥራች አባላት እና አዲስ አክሲዮኑን ለመግዛት ዝግጁ የሆኑ ወንድሞች እና እህቶች ለመግዛት ጊዜው እንዳጠረባቸው ባሉን የመገናኛ መንገዶች በሙሉ በተደጋጋሚ ጠይቀውናል፡፡ ለዚህም መልስ መስጠት በጣም አስፈላጊ መሆኑንና እንዲሁም ባለፈው ተፈጥሮ በነበረው ሀገራዊ ችግር ምክንያት ያልደረስንባቸው ቦታዎች ላይ መድረስ አስፈላጊ በመሆኑ ቀኑን ማራዘም የተሻለ መሆኑ ታምኖበታል፡፡ በተጨማሪም መቅረዝ ሰፊ የኅብረተሰብ መሠረት እንዲኖረው የቦርዱ ጽኑ ፍላጎት ነው፡፡ በመሆኑም አጠቃላይ የአክሲዮን ሽያጩን እስከ መጋቢት 30 2013 ዓ.ም ያራዘመ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አፈጻጸሙን በተመለከተ ሲናገሩ ለመጀመሪያው አንድ ወር ከ 20 ሺህ ብር ጀምሮ አክሲዮን የሚገዙ በሙሉ መሥራች መሆን እንደሚችል፤ ከ መጋቢት አንድ እስከ አስራ አምስት ግን ይኽ መነሻ ዋጋ በብር 10 ሺህ ጨምሮ 30 ሺህ ብር እንደሚሆን፤ በቀጣይ 15 ቀናት እስከ መጋቢት 30 ደግሞ የመሥራችነት ጥቅም የሚያስገኘው የአክሲዮን ሽያጭ አርባ ሺህ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡ ይኸ ማለት በ ሃያ ሺህ ብር መግዛት ይከለከላል ሳይሆን የመሥራችነት ጥቅም ግን አያገኙም ለማለት ነው፡፡ስለዚህ ብዙኀኑ እንዲሳተፍ የተራዘመውን የአክሲዮን ሽያጭ በአግባቡ እንጠቀምበት፤ ሌሎች አላማውን አውቀው እንዲሳተፉ እንድንቀሰቅስ የሚል መልእክትን አስተላልፈዋል፡፡
በመጨረሻም በቅርቡ የኢሜጂንግ ዲያግኖስቲኩን ሥራ ለማስጀመር የሚያስፈልጉ ቅድመ ዝግጅቶችን ቡድኑ እያጠናቀቀ መሆኑን እና በተቻለ ፍጥነት ወደ ትግበራ ለመግባት በዝግጅት ላይ እንዳሉ ገልጸዋል፡፡